ትንቢተ ኢሳይያስ 60
60
የወደፊቱ የኢየሩሳሌም ክብር
1ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ብርሃንሽ መጥቶአልና፥ የእግዚአብሔርም ብርሃን በአንቺ ላይ ወጥቶአልና አብሪ፤ አብሪ።#ዕብ. “ተነሺ” ይላል። 2እነሆ፥ ጨለማ ምድርን፥ ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል፤ ነገር ግን በአንቺ ላይ እግዚአብሔር ይገለጣል፤ ክብሩም በአንቺ ላይ ይታያል፤ 3ነገሥታት በብርሃንሽ፥ አሕዛብም በፀዳልሽ ይሄዳሉ።
4ዐይኖችሽን አንሥተሽ በዙሪያሽ ተመልከቺ፤ ልጆችሽም እንደ ተሰበሰቡ እነሆ፥ እዪ፤ ወንዶች ልጆችሽ ከሩቅ ይመጣሉ፤ ሴቶች ልጆችሽንም በጫንቃ ላይ ይሸከሙአቸዋል። 5በዚያ ጊዜ አይተሽ ትፈሪያለሽ፤ የአሕዛብና የሀገሮች ብልጽግና ወደ አንቺ ይመለሳልና፥#ዕብ. “የባሕሩ በረከት ወደ አንቺ ስለሚመለስ የአሕዛብም ብልጥግና ወደ አንቺ ስለሚመጣ አይተሽ ደስ ይልሻል” ይላል። ልብሽ ይደነግጣል። 6የግመሎች መንጋ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የምድያምና የኤፋ ግመሎች ይሸፍኑሻል፤ ሁሉ ከሳባ ወርቅንና ዕጣንን ይዘው ይመጣሉ፤ የእግዚአብሔርንም ማዳን ያበሥራሉ። 7የቄዳር በጎች ሁሉ ወደ አንቺ ይሰበሰባሉ፤ የነባዮትም አውራ በጎች ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ በመሠዊያዬ ላይም የተመረጠው መሥዋዕት ይቀርባል፤ የጸሎቴ#ዕብ. “የክብሬንም ቤት አከብራለሁ” ይላል። ቤትም ይከብራል። 8እንደ ደመና፥ ከጫጩቶችዋ ጋር ወደ መስኮቷ እንደምትገባ ርግብም የሚበርሩ እነዚህ እነማን ናቸው? 9ደሴቶች እኔን ተስፋ ያደርጋሉ፤ የተርሴስም መርከቦች አስቀድመው ይመጣሉ፤ ልጆችሽ ስለ ከበረው ስለ እስራኤል ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ስም ወርቅና ብር ይዘው ከሩቅ ሀገር ይመጣሉ።
10በቍጣዬ ቀሥፌ በይቅርታዬ አቅርቤሻለሁና መጻተኞች ቅጥርሽን ይሠራሉ፤ ነገሥታቶቻቸውም በፊትሽ ይቆማሉ። 11በሮችሽም ሁልጊዜ ይከፈታሉ፤ ሰዎች የአሕዛብን ብልጽግና፥ የተማረኩትንም ነገሥታቶቻቸውን ወደ አንቺ ያመጡ ዘንድ ሌሊትና ቀን አይዘጉም። 12ለአንቺም የማይገዙ ነገሥታት ይሞታሉ፤ እነዚያም አሕዛብ ፈጽመው ይጠፋሉ። 13የመቅደሴንም ስፍራ ያከብሩ ዘንድ የሊባኖስ ክብር፥ ጥዱና አስታው፥ ባርሰነቱም ወደ አንቺ ይመጣሉ፥ 14የአስጨናቂዎችሽም ልጆች እየተንቀጠቀጡ ወደ አንቺ ይመጣሉ፤ የናቁሽም ሁሉ ወደ እግርሽ ጫማ ይሰግዳሉ፤ የእስራኤል ቅዱስ የእግዚአብሔር ከተማ፥ ጽዮን ተብለሽም ትጠሪያለሽ።
15የተተውሽና የተጠላሽ ሆነሻልና የሚረዳሽ አጣሽ፤ ነገር ግን የዘለዓለም ደስታን ለልጅ ልጅ እሰጥሻለሁ። 16የአሕዛብንም ወተት ትጠጫለሽ፤ የነገሥታትንም ብልጽግና ትበያለሽ፤ እኔም እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ፥ መድኀኒትሽና ታዳጊሽ እንደ ሆንሁ ታውቂያለሽ። 17በናስ ፋንታ ወርቅን፥ በብረትም ፋንታ ብርን፥ በእንጨትም ፋንታ ናስን፥ በድንጋይም ፋንታ ብረትን እሰጥሻለሁ። ለአለቆችሽም ሰላምን፥ ለመኳንንትሽም ፍርድን አደርጋለሁ፤ 18እንግዲህ በምድርሽ ውስጥ ግፍ፥ በዳርቻሽም ውስጥ ጕስቍልናና ቅጥቃጤ አይሰማም፤ ቅጥሮችሽ ድኅነት ይባላሉ፤ በሮችሽም በጥርብ ድንጋይ ይሠራሉ። 19ፀሐይ በቀን የሚያበራልሽ አይደለም፤ በሌሊትም ጨረቃ የሚወጣልሽ አይደለም፤ ለአንቺስ እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ፥ አምላክሽም ክብርሽ ይሆናል። 20እግዚአብሔር የዘለዓለም ብርሃንሽ ይሆናልና፥ የልቅሶሽም ወራት ያልፋልና፤ ፀሐይሽ ከዚህ በኋላ አትጠልቅም፤ ጨረቃሽም አይቋረጥም። 21ሕዝብሽ ሁሉ ጻድቃን ይሆናሉ፤ ምድርንም ለዘለዓለም ይወርሳሉ፤ እርሱንም ለማመስገን የእጆቹን ሥራ ይጠብቃሉ። 22ታናሹ ሺህ፥ የሁሉም ታናሽ ታላቅ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመናቸው ሁሉ እሰበስባቸዋለሁ።
Currently Selected:
ትንቢተ ኢሳይያስ 60: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapistaging.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ