መጽሐፈ መሳፍንት 8
8
የጌዴዎን የመጨረሻው ድል
1የኤፍሬም ሰዎችም፥ “ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? ምድያምን ለመዋጋት በወጣህ ጊዜ ለምን አልጠራኸንም?” አሉት። ጽኑ ጥልም ተጣሉት። 2እርሱም፥ “እኔ ዛሬ እናንተ እንዳደረጋችሁት ምን አደረግሁ? የኤፍሬም ወይን ቃርሚያ ከአቢዔዜር ወይን መከር አይሻልምን? 3እግዚአብሔር የምድያምን አለቆች ሔሬብንና ዜብን በእጃችሁ አሳልፎ ሰጥቶአቸዋል እናንተ ያደረጋችሁትን የሚመስል እኔ ምን ማድረግ እችል ኖርአል?” አላቸው። ከዚህ በኋላ ተዉት፤ ይህን ቃል በተናገራቸውም ጊዜ መንፈሳቸው ዐረፈች።
4ጌዴዎንም ወደ ዮርዳኖስ መጥቶ ተሻገረ፤ ከእርሱም ጋር ያሉት ሦስት መቶ ሰዎች ተሻገሩ፤ ምንም እንኳ ቢራቡም ያሳድዱ ነበር። 5የሱኮትንም ሰዎች፥ “ተርበዋልና እኔን ለተከተሉ ሰዎች እባካችሁ እህል ስጡአቸው፤ እኔም የምድያምን ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን አሳድዳለሁ” አላቸው። 6የሱኮትም አለቆች፥ “እኛ ለሠራዊትህ እህል እንድንሰጥ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን?” አሉ። 7ጌዴዎንም፥ “እግዚአብሔር ዛብሄልንና ስልማናን በእጄ አሳልፎ ቢሰጠኝ እኔ በምድረ በዳ እሾህና በኩርንችት ሥጋችሁን እገርፋለሁ” አለ። 8ከዚያም ወደ ፋኑሄል ወጣ፤ ለፋኑሄልም ሰዎች እንዲሁ አላቸው፤ የፋኑሄልም ሰዎች የሱኮት ሰዎች እንደ መለሱ መለሱለት። 9እርሱም የፋኑሄልን ሰዎች፥ “በደኅና በተመለስሁ ጊዜ ይህን ግንብ አፈርሰዋለሁ” ብሎ ተናገራቸው።
10ዛብሄልና ስልማናም ከሠራዊቶቻቸው ጋር በቀርቀር ነበሩ፤ ሰይፍ የሚመዝዙ መቶ ሃያ ሺህ ሰዎች ወድቀው ነበርና ከምሥራቅ ሰዎች ሠራዊት ሁሉ የቀሩ ዐሥራ አምስት ሺህ ያህል ሰዎች ነበሩ። 11ጌዴዎንም በድንኳን የሚኖሩ ሰዎች ባሉበት መንገድ በኖቤትና በዮግቤል#“በዮግቤል” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ብቻ። በምሥራቅ በኩል ወጣ፤ ሠራዊቱም ተዘልሎ ሳለ አጠፋቸው። 12ዛብሄልና ስልማናም ሸሹ፤ እርሱም አሳደዳቸው፤ ሁለቱንም የምድያም ነገሥታት ዛብሄልንና ስልማናን ያዘ፤ ጌዴዎንም ሠራዊቱን ሁሉ አጠፋ።
13የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎንም ከአሬስ ዳገት ከጦርነት ተመለሰ። 14ከሱኮትም ሰዎች አንድ ብላቴና ይዞ መረመረው፤ እርሱም ሰባ ሰባቱን የሱኮትን አለቆችና ሽማግሌዎችን አስቈጠራቸው። 15ጌዴዎንም ወደ ሱኮት አለቆች መጥቶ፥ “ለደከሙት ሰዎችህ እህል እንሰጥ ዘንድ የዛብሄልና የስልማና እጅ አሁን በእጅህ ነውን? ብላችሁ የተላገዳችሁብኝ፥ ዛብሄልና ስልማና እነሆ፥” አለ። 16የከተማዪቱንም ሽማግሌዎችና አለቆች ያዘ፥ የምድረ በዳንም እሾህና ኩርንችት ወስዶ የሱኮትን ሰዎች ገረፋቸው። 17የፋኑሄልንም ግንብ አፈረሰ፤ የከተማዪቱንም ሰዎች ገደላቸው።
18ዛብሄልንና ስልማናን፥ “በታቦር የገደላችኋቸው ሰዎች እንዴት ያሉ ነበሩ?” አላቸው፤ እነርሱም፥ “እንዳንተ ያሉ ነበሩ፤ አንተንም ይመስሉ ነበር፤ መልካቸውም እንደ ነገሥት ልጆች መልክ ነበረ” ብለው መለሱለት። 19ጌዴዎንም፥ “የእናቴ ልጆች ወንድሞቼ ነበሩ፤ አድናችኋቸው ቢሆን ኖሮ፥ ሕያው እግዚአብሔርን! እኔ አልገድላችሁም ነበር” አለ። 20በኵሩንም ዮቶርን፥ “ተነሥተህ ግደላቸው” አለው፤ ብላቴናው ግን ገና ትንሽ ነበረና ስለ ፈራ ሰይፉን አልመዘዘም። 21ዛብሄልና ስልማናም፥ “ኀይልህ እንደ ጐልማሳ ኀይል ነውና አንተ ተነሥተህ ውደቅብን” አሉት። ጌዴዎንም ተነሥቶ ዛብሄልንና ስልማናን ገደለ፤ በግመሎቻቸውም አንገት የነበሩትን ሥሉሴዎች ማረከ።
22የእስራኤልም ሰዎች ጌዴዎንን፥ “ከምድያም እጅ አድነኸናልና አንተ፥ ልጅህም፥ የልጅ ልጅህም#“የልጅ ልጅህም” የሚለው በዕብ. እና በግሪክ ሰባ. ሊ. ብቻ። ደግሞ ግዙን” አሉት። 23ጌዴዎንም፥ “እኔ አልገዛችሁም፤ ልጄም አይገዛችሁም፤ እግዚአብሔር ይገዛችኋል እንጂ” አላቸው። 24እስማኤላውያንም ስለ ነበሩ የወርቅ ጕትቻ ነበራቸውና ጌዴዎን፥ “ሁላችሁም ከምርኮአችሁ ጕትቻችሁን እንድትሰጡኝ እለምናችኋለሁ” አላቸው። 25እነርሱም፥ “መስጠትን ፈቅደን እንሰጥሃለን” ብለው መለሱለት። መጐናጸፊያም አነጠፉ፤ ሰውም ሁሉ የምርኮውን ጕትቻ በዚያ ላይ ጣለ። 26የለመነውም የወርቅ ጕትቻ ሚዛኑ ከአምባሩ፥ ከድሪውም፥ የምድያምም ነገሥታት ከለበሱት ከቀዩ ቀሚስ፥ በግመሎቻቸውም አንገት ከነበሩት ሥሉሴዎች ሌላ ሺህ ሰባት መቶ ሰቅለ ወርቅ ነበረ። 27ጌዴዎንም ምስል#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኤፉድ” ይላል። አድርጎ ሠራው፤ በከተማውም በኤፍራታ አኖረው፤ እስራኤልም ሁሉ ተከትሎ አመነዘረበት፤ ለጌዴዎንና ለቤቱም ወጥመድ ሆነ። 28ምድያምም በእስራኤል ልጆች ተዋረዱ፤ ራሳቸውንም ዳግመኛ አላነሡም፤ በጌዴዎንም ዕድሜ ምድሪቱ አርባ ዓመት ዐረፈች።
የጌዴዎን ሞት
29የኢዮአስም ልጅ ይሩበኣል ሄዶ በቤቱ ተቀመጠ። 30ለጌዴዎንም ብዙ ሚስቶች ነበሩትና ከአብራኩ የወጡ ሰባ ልጆች ነበሩት። 31በሴኬምም የነበረችው ዕቅብቱ ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ስሙንም አቤሜሌክ ብሎ ጠራው። 32የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ በአብያዜራውያንም ከተማ በኤፍራታ በነበረችው በአባቱ በኢዮአስ መቃብር ተቀበረ።
33እንዲህም ሆነ፤ ጌዴዎን ከሞተ በኋላ የእስራኤል ልጆች ተመለሱ፤ በዓሊምንም ተከትለው አመነዘሩ፤ በዓሊምም አምላክ ይሆናቸው ዘንድ ከእርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገቡ። 34የእስራኤልም ልጆች በዙሪያቸው ከነበሩት ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ ያዳናቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን አላሰቡትም፤ 35እርሱም ለእስራኤል በጎ ነገርን ሁሉ እንዳደረገ መጠን፥ እነርሱ ይሩበኣል ለተባለው ለጌዴዎን ቤት ወረታ አላደረጉም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መሳፍንት 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ