ኦሪት ዘኍልቍ 35
35
ለሌዋውያን የተሰጡ ከተሞች
1እግዚአብሔርም ሙሴን በዮርዳኖስ አጠገብ በኢያሪኮ አንጻር በሞዓብ ምዕራብ እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 2“ሌዋውያን የሚቀመጡባቸውን ከተሞች ከሚካፈሉት ርስታቸው ይሰጡ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው፤ በከተሞቹም ዙሪያ ያሉትን መሰማሪያዎች ለሌዋውያን ይስጡአቸው። 3ከተሞቹም ለእነርሱ መኖሪያ ይሆናሉ፤ መሰማርያቸውም ለከብቶቻቸውና ለእንስሶቻቸው ይሁን። 4ለሌዋውያንም የምትሰጡት የከተማ መሰማርያ በከተማው ዙሪያ ከቅጥሩ ወደ ውጭ አንድ ሺህ ክንድ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሁለት ሺህ ክንድ” ይላል። ይሁን። 5ከከተማው ውጭ በምሥራቅ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በደቡብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በምዕራብ በኩል ሁለት ሺህ ክንድ፥ በሰሜንም በኩል ሁለት ሺህ ክንድ ትከነዳላችሁ፤ ከተማውም በመካከል ይሆናል፤ ይህም የከተሞቹ መሰማርያ ይሆንላቸዋል። 6ለሌዋውያንም ከተሞችን ትሰጣላችሁ፤ ከምትሰጡአቸውም ከተሞች ስድስቱ ነፍሰ ገዳይ የሚሸሽባቸው የመማፀኛ ከተሞች ናቸው፤ ከእነዚህ ሌላ አርባ ሁለት ከተሞችን ትሰጣላችሁ። 7ለሌዋውያን የምትሰጡአቸው ከተሞች ሁሉ አርባ ስምንት ከተሞች ይሆናሉ፤ እነዚህም ከመሰማርያዎቻቸው ጋር ናቸው። 8ከእስራኤል ልጆች ርስት ለሌዋውያን የምትሰጡአቸውን ከተሞች እንዲህ ስጡ፤ ከብዙዎቹ ብዙ፥ ከጥቂቶቹ ጥቂት ትወስዳላችሁ፤ እያንዳንዱ እንደ ወረሱት እንደ ርስታቸው መጠን ከከተሞቻቸው ለሌዋውያን ይሰጣሉ።”
የመማፀኛ ከተሞች
(ዘዳ. 19፥1-13፤ ኢያ. 20፥1-9)
9እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10“ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ 11እነሆ፥ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ ባላማወቅ ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንተ ለዩ። 12ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስከሚቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 13የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። 14በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞችን ትለያላችሁ፤ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞችን ትለያላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞችም ይሆናሉ። 15ባለማወቅ ነፍስ የገደለ ሁሉ ይሸሽባቸው ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች፥ በመካከላቸውም ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ።
16“በብረት መሣሪያ ቢመታው፥ ቢሞትም ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 17ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው፥ የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 18ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣሪያ ቢመታው፥ የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። 19ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው። 20ጥል ቢጣላው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ቢሞትም፥ 21ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ባለ ደሙ ወይም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው።
22“ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ 23ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ 24ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥ ማኅበሩ በመቺውና በባለ ደሙ መካከል ፍርድን እንደዚህ ይፍረዱ፤ 25ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከባለ ደሙ እጅ ያድኑታል፤ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛው ከተማ ይመልሱታል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። 26ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥ ባለ ደሙም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ 27ባለ ደሙም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ በደል የለበትም፤ 28ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ታላቁ ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል።
29“እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዐትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። 30ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች ቃል ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። 31ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። 32ታላቁ ካህን እስኪሞት ወደ ምድሩ ትመልሱት ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው ዋጋ አትቀበሉ። 33ምድርን የሚያረክሳት ደም ነውና የምትኖሩባትን ምድር በነፍስ ግድያ አታርክሷት። ምድሪቱም በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። 34እናንተ በውስጥዋ የምትኖሩባትን፥ እኔም ከእናንተ ጋር የማድርባትን ምድር አታርክሱኣት፤ በእስራኤል ልጆች መካከል የማድር እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
Currently Selected:
ኦሪት ዘኍልቍ 35: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ