መጽሐፈ ጥበብ 5
5
1ያንጊዜ ጻድቁ፦ መከራ ባጸኑበትና ድካሙን በካዱ፥ ነገሩንም በናቁ ሰዎች ፊት በብዙ መገለጥ ይቆማል። 2በግርማና በክፉ ማስፈራራት ሆኖ ባዩት ጊዜ ይታወካሉ፤ ድንቅ ስለሚሆን ደኅንነቱም ይደነቃሉ። 3እየተጸጸቱና በተጨነቀ መንፈስ እየጮኹ እርስ በርሳቸው ይናገራሉ፦ እንዲህም ይላሉ፥ “ቀድሞ በኛ በሰነፎች ዘንድ መሣቂያና ማሽሟጠጫ የሆነው፥ 4ሥራውን ስንፍና፥ ሞቱንም የተናቀ ያደረግንበት ይህ ነውን? 5እንዴት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ? ርስቱስ እንዴት ለቅዱሳን ሆነች? 6ስለዚህ ከቀና መንገድ ወጥተን ስተናል፥ የጽድቅ ብርሃንም አልተገለጠልንም፥ ፀሐይም አልወጣልንም። 7በደልንና ጥፋትን በመንገዳችን ሞላን፤ በምድረ በዳም ሄድን፤ የእግዚአብሔርንም መንገድ አላወቅንም።
8“ትዕቢት ምን ጠቀመን? ከትዕቢት ጋር ያለ ባለጠግነትስ ምን አመጣልን? 9ይህ ሁሉ እንደ ጥላ ኀላፊ ነው፤ ፈጥኖም እንደሚሄድ ወሬ ነው። 10በባሕር ላይ እንደሚሄድ፥ ውኃም በማዕበሉ እንደሚነጥቀው፥ ያለፈበት ፍለጋው እንደማይገኝ፥ በማዕበሉም መካከል አካሉ የሄደበት መንገድ እንደማይታወቅ መርከብ፥ 11በአየር ላይ የሚበርር ዎፍ የሄደበት ፍለጋው እንደማይገኝ፥ በበረረ ጊዜ ቀላሉን አየር እየከፈለ ፈጥኖ ይሄዳልና፥ ክንፉንም እያርገበገበ፥ ፈጥኖ ይበርራልና ከሄደም በኋላ በነፋሱ ውስጥ ያለፈበት ምልክቱ እንደማይገኝ፥ 12ይህም ባይሆን የተወረወረ ፍላፃ ሰንጥቆት ያለፈው አየር ተመልሶ እንደሚገጥም፥ በአየር ውስጥ የሄደበትም እንደማይታወቅ፥ 13እኛም እንዲሁ ነን፤ በተወለድን ጊዜ ጠፋን። በክፋታችን ጠፋን እንጂ በጎ ምልክትን እናሳይ ዘንድ አልተገባንም።”
14የክፉዎች ሰዎች ተስፋቸው ነፋስ እንደሚበትነው ትቢያ፥ በነፋስ ቀልጦ እንደሚጠፋ ረቂቅ ውርጭ፥ በነፋስም ተበትኖ እንደሚጠፋ ጢስ፥ አንድ ቀንም አድሮ እንደሚሄድ መጻተኛ ስም አጠራር ነው።
ጻድቃን የሚያገኙትዋጋ
15ጻድቃን ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ፤ ዋጋቸውም በእግዚአብሔር ዘንድ የጸና ነው፤ ጥበቃቸውም በልዑል ዘንድ ነው። 16ስለዚህም የክብር መንግሥትንና ጌጥ ያለው አክሊልን ከእግዚአብሔር እጅ ይቀበላሉ፤ በቀኙ ይሰውራቸዋልና፥ በክንዱም ይረዳቸዋልና። 17ፍጹም የሆነ የቅንዐቱን ጦር መሣሪያ ይይዛል፤ ጠላቶቹንም ለመበቀል ፍጥረቱን የጦር መሣሪያ ያደርጋታል። 18የጽድቅ ጥሩርንም ይለብሳል፥ ማድላት የሌለበት የፍርድ ራስ ቍርንም ይቀዳጃል። 19የማይሸነፍ የእውነት ጋሻንም ይይዛል። 20መዓቱንም እንደሚቈርጥ ሰይፍ ይስላል፤ ዓለምም ከእርሱ ጋር ሆኖ አላዋቂዎችን ይዋጋል። 21ፈጥኖ ያገኛቸው ዘንድ በአሳቾች ሰዎች ላይ የመብረቆቹ ድል ነጎድ በቀጥታ ይሄድባቸዋል። መልካም ሆኖ ከተገተረ ቀስት እንደሚወረወር ፍላጻ ከደመናዎች ውስጥ ወደ ዓላማቸው ይወረወራሉ ። 22ከመዓቱ ድል ነጎድ ደንጊያም ፈጥኖ በረዶን ያወርዳል፤ የባሕሩም ውኃ በእነርሱ ላይ ይበሳጭባቸዋል፤ ፈሳሾችም ይነዋወጣሉ፤ ፈጥነውም ይከቧቸዋል። 23ኀይል ያለው ነፋስም ይቃወማቸዋል፤ እንደ ነፋስም ያደርቃቸዋል፤ ኀጢአት ምድሩን ሁሉ ታጠፋለችና፥ ክፉም መሥራት የኀያላኑን ዙፋን ይገለብጣልና ይበትናቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ጥበብ 5: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ