ኦሪት ዘፍጥረት 17
17
የቃል ኪዳን እና መገረዝ
1አብራምም የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው በሆነ ጊዜ ጌታ ለአብራም ተገለጠለትና፦ “እኔ ኤልሻዳይ ነኝ፥ በፊቴ ተመላለስ፥ ፍጹምም ሁን፥ 2ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል አደርጋለሁ፥ እጅግም አበዛሃለሁ” አለው። 3አብራምም በግምባሩ ወደቀ፥ እግዚአብሔርም እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “እነሆ፥ ቃል ኪዳኔ ከአንተ ጋር ነው፥ 4ለብዙ አሕዛብም አባት ትሆናለህ። 5#ሮሜ 4፥17።ከዛሬም ጀምሮ እንግዲህ ስምህ አብራም ተብሎ አይጠራ፥ ነገር ግን ስምህ አብርሃም ይሆናል፥ ለብዙ አሕዛብ አባት አድርጌሃለሁና። 6እጅግም አበዛሃለሁ፥ ሕዝብም አደርግሃለሁ፥ ነገሥታትም ከአንተ ይወጣሉ። 7#ሉቃ. 1፥55።ቃል ኪዳኔንም በእኔና በአንተ መካከል ከአንተም በኋላ ከዘርህ ጋር በትውልዳቸው ለዘለዓለም ኪዳን አቆማለሁ፥ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ አምላክ እሆን ዘንድ። 8#የሐዋ. 7፥5።በእንግድነት የምትኖርባትን ምድር፥ የከነዓን ምድር ሁሉ፥ ለዘለዓለም ግዛት ይሆንህ ዘንድ ለአንተና ከአንተ በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።”
9እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፥ አንተ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው። 10#የሐዋ. 7፥8፤ ሮሜ 4፥11።በእኔና በአንተ መካከል፥ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቁት ቃል ኪዳኔ ይህ ነው፥ በመካከላችሁ ያለ ወንድ ሁሉ ይገረዝ።#17፥10 መገረዝ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር ያደረገው የኪዳን ምልክት ነበር። ዘፍ. 34፥14፤ ዘጻ. 4፥24-26፤ ሌዋ. 19፥23፤ እዚህ ላይ ልክ እንደ “ቀስተ ደመና ምልክት” ሆነ፥ ዘፍ. 9፥16-17። በእግዚአብሔር ቃል ኪዳንና ከተመረጡ የሰው ልጆች ከእኔነት የመነጨ ግዴታ የሚያስታውስ ነው። ይልቁንም እነዚህ የሕግ መጻሕፍት ሁለት አጋጣሚዎችን ብቻ ያቀርባሉ። ዘፍ. 12፥44፤ ዘጻ. 12፥3፤ ኢያ. 5፥2-8፤ በግዞት ብቻና ከዚያ በኋላ ሙሉ ስመጥርነቱን አገኘ። 1መቃ. 1፥63፤ 2መቃ. 6፥10፤ ቅዱስ ጳውሎስም “የእምነት ማረጋገጫ ምልክት ብሎታል” ሮሜ. 4፥11 “የልብ መገረዝን” ኤር. 4፥4 ተመልከት። 11የቍልፈታችሁንም ሥጋ ትገረዛላችሁ፥ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል። 12የስምንት ቀን ልጅ ይገረዝ፥ በቤት የተወለደ ወይም ከዘራችሁ ያልሆነ በብርም ከእንግዳ ሰው የተገዛ፥ ወንድ ሁሉ በትውልዳችሁ ይገረዝ። 13በቤትህ የተወለደ በብርህም የተገዛ ፈጽሞ ይገረዝ። ቃል ኪዳኔም በሥጋችሁ የዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆናል። 14የቍልፈቱን ሥጋ ያልተገረዘ ቈላፍ ሰው ሁሉ፥ ያች ነፍስ ከወገንዋ ተለይታ ትጥፋ፥ ቃል ኪዳኔን አፍርሳለችና።”
15እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፦ “የሚስትህን የሦራን ስም ‘ሦራ’ ብለህ አትጥራ፥ ስምዋ ሣራ ይሆናል እንጂ። 16እባርካታለሁ፥ ደግሞም ከእርሷ ልጅ እሰጥሃለሁ፥ እባርካታለሁም፥ የአሕዛብም እናት ትሆናለች፥ የአሕዛብ ነገሥታት ከእርሷ ይወጣሉ።” 17አብርሃምም በግምባሩ ወደቀ፥ ሳቀም፥ በልቡም አለ፦ “የመቶ ዓመት ሰው በውኑ ልጅ ይወልዳልን? ዘጠና ዓመት የሆናትም ሣራ ትወልዳለችን?” 18አብርሃምም እግዚአብሔርን፥ “እስማኤል በፊትህ ቢኖር በወደድሁ ነበር” አለው። 19እግዚአብሔርም አለ፦ “በእውነት ሚስትህ ሣራ ወንድ ልጅን ትወልድልሃለች፥ ስሙንም ይስሐቅ ብለህ ትጠራዋለህ፥ ከእርሱ በኋላ ለዘሩ የዘለዓለም ቃል ኪዳን እንዲሆን ቃል ኪዳኔን ከእርሱ ጋር አቆማለሁ። 20ስለ እስማኤልም ሰምቼሃለሁ፥ እነሆ ባርኬዋለሁ፥ ፍሬያምም አደርገዋለሁ፥ እጅግም አበዛዋለሁ፥ ዐሥራ ሁለት አለቆችንም ይወልዳል፥ ታላቅ ሕዝብም እንዲሆን አደርገዋለሁ። 21ቃል ኪዳኔን ግን በሚመጣው ዓመት በዚሁ ጊዜ ሣራ ከምትወልድልህ ከይስሐቅ ጋር አቆማለሁ።”
22ንግግሩንም ከእርሱ ጋር በፈጸመ ጊዜ እግዚአብሔር ከአብርሃም ተለይቶ ወጣ። 23አብርሃምም ልጁን እስማኤልን፥ በቤቱም የተወለዱትን ሁሉ፥ በብሩም የገዛቸውን ሁሉ፥ ከአብርሃም ቤተሰብ ወንዶቹን ሁሉ ወሰደ፥ የቍልፈታቸውንም ሥጋ እግዚአብሔር እንዳለው በዚያው ቀን ገረዘ። 24አብርሃምም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሰው ነበረ፥ 25ልጁ እስማኤልም የቍልፈቱን ሥጋ በተገረዘ ጊዜ የዐሥራ ሦስት ዓመት ልጅ ነበረ። 26በዚያው ቀን አብርሃም ተገረዘ፥ ልጁ እስማኤልም። 27በቤት የተወለዱትና በብር ከእንግዶች የተገዙት፥ የቤቱ ሰዎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ተገረዙ።
موجودہ انتخاب:
ኦሪት ዘፍጥረት 17: መቅካእኤ
سرخی
شئیر
کاپی
کیا آپ جاہتے ہیں کہ آپ کی سرکیاں آپ کی devices پر محفوظ ہوں؟ Sign up or sign in