እግዚአብሔር ኖኅንና በመርከቧ ውስጥ ከርሱ ጋራ የነበሩትን የዱርና የቤት እንስሳት ሁሉ ዐሰበ፤ በምድር ላይ ነፋስ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም ጐደለ። የጥልቁ ምንጮችና የሰማይ ውሃ መስኮቶች ተዘጉ፤ ዝናቡም መዝነቡን አቆመ። ውሃው ከምድር ላይ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መጣ፤ ከመቶ ዐምሳ ቀን በኋላም ጐደለ። በሰባተኛው ወር፣ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ ዐረፈች። ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ እየቀነሰ መጣ፤ በዐሥረኛው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቧን መስኮት ከፍቶ፣ ቍራን ወደ ውጭ ላከ፤ ቍራውም ውሃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚያም በኋላ፣ ኖኅ ውሃው ከምድር ገጽ ጐድሎ እንደ ሆነ ለማወቅ ርግብን ላከ፤ ነገር ግን ውሃው የምድርን ገጽ ገና እንደ ሸፈነ ስለ ነበር፣ ተመልሳ ኖኅ ወዳለበት መርከብ መጣች፤ እርሱም እጁን ዘርግቶ ተቀበላት፤ ወደ መርከቢቱም አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቧን እንደ ገና ላካት። እርሷም ወደ ማታ ተመለሰች፤ እነሆም የለመለመ የወይራ ቅጠል በአፏ ይዛ ነበር፤ ያን ጊዜ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጕደሉን ዐወቀ። ሰባት ቀንም ቈይቶ ርግቧን እንደ ገና ላካት፤ በዚህ ጊዜ ግን ርግቧ ወደ እርሱ አልተመለሰችም። ኖኅ በተወለደ በስድስት መቶ አንደኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ። ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፤ የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ። በሁለተኛው ወር፣ በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ደረቀች። ከዚያም እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “አንተና ሚስትህ፣ ልጆችህና የልጆችህ ሚስቶች ከመርከቧ ውጡ። እንዲዋለዱ፣ እንዲራቡና በምድር ላይ እንዲበዙ፣ ከአንተ ጋራ ያሉትን ወፎች፣ እንስሳትና በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታትን ሁሉ ይዘሃቸው ውጣ።” ኖኅም ከልጆቹ፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ሚስቶች ጋራ ወጣ። እንስሳቱ ሁሉ፣ ወፎችም፣ በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጥረታት ሁሉ በየወገናቸው ከመርከቧ ወጡ። ከዚያም ኖኅ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ መሠዊያው ላይ ንጹሕ ከሆኑት እንስሳት ሁሉ፣ እንዲሁም ንጹሕ ከሆኑት ወፎች የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርም ደስ የሚያሠኘውን መዐዛ አሸተተ፤ በልቡም እንዲህ አለ፤ “ምንም እንኳ ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ ቢሆንም በርሱ ምክንያት ሁለተኛ ምድርን አልረግማትም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕያዋን ፍጥረታትን ዳግመኛ አላጠፋም። “ምድር እስካለች ድረስ፣ የዘር ወቅትና መከር፣ ሙቀትና ቅዝቃዜ በጋና ክረምት፣ ቀንና ሌሊት፣ አይቋረጡም።”
ዘፍጥረት 8 ያንብቡ
ያዳምጡ ዘፍጥረት 8
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ዘፍጥረት 8:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች