ኦሪት ዘፍጥረት 8:1-22

ኦሪት ዘፍጥረት 8:1-22 አማ05

እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ፤ ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፤ ውሃውም መጒደል ጀመረ። ከምድር በታች ያሉት ጥልቅ ምንጮች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ መጒደል ጀመረ፤ ከመቶ ኀምሳ ቀኖችም በኋላ ውሃው ከምድር ላይ በጣም ጐደለ። በሰባተኛው ወር፥ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን መርከቡ “አራራት” ከተባሉት ተራራዎች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈ። ውሃው እስከ ዐሥረኛው ወር ድረስ ቀስ በቀስ እየጐደለ ሄደ፤ በዐሥረኛው ወር መጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ታዩ። ከአርባ ቀን በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቡን መስኮት ከፈተ፤ ቊራን ወደ ውጪ ላከው፤ ቊራውም ውሃው ከምድር እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጒደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። እርስዋም ወደ ማታ ጊዜ የለመለመ የወይራ ዘይት ዛፍ ቅጠል በአፍዋ ይዛ ወደ ኖኅ ተመለሰች፤ በዚህ ሁኔታ ኖኅ ውሃው ከምድር መጒደሉን ዐወቀ። ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ኖኅ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ በዚህን ጊዜ ግን ርግቢቱ ሳትመለስለት ቀረች። የኖኅ ዕድሜ 601 ዓመት በሆነ ጊዜ በመጀመሪያው ወር፥ በመጀመሪያው ቀን ውሃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፤ ምድሪቱ እንደ ደረቀች አየ። በሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ ሰባተኛው ቀን ምድር ፈጽማ ደረቀች። እግዚአብሔር ኖኅን እንዲህ አለው፤ “አንተ ከሚስትህ፥ ከልጆችህና ከልጆችህ ሚስቶች ጋር ሆነህ ከመርከቡ ውጣ፤ ተራብተውና ተባዝተው ምድርን ሁሉ እንዲሞሉ ከአንተ ጋር ያሉትን ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ወፎችን፥ እንስሶችንና ሌሎችን በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ ይዘህ ውጣ።” ከዚህ በኋላ ኖኅ ከሚስቱ፥ ከልጆቹና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ሆኖ ከመርከቡ ወጣ፤ አራዊትና እንስሶች፥ ወፎችም በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችም በየወገናቸው ሆነው ከመርከቡ ወጡ። ኖኅ ለእግዚአብሔር መሠዊያን ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ከየዐይነቱ አንዳንድ ወሰደ፤ መሥዋዕት እንዲሆኑም ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠላቸው። የመሥዋዕቱም መዓዛ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው፤ በሐሳቡም እንዲህ አለ፥ ገና ከሕፃንነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው ሐሳብ ክፉ መሆኑን ስለማውቅ፤ “ሰው በሚፈጽመው በደል ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም፤ በአሁኑ ጊዜ እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም። ምድር እስካለች ድረስ፥ ለመዝራትና ለማጨድ፥ ለብርድና ለሙቀት፥ ለበጋና ለክረምት፥ ለቀንና ለሌሊት የማያቋርጥ ጊዜ ይኖራል።”