ኦሪት ዘፍጥረት 8:1-22

ኦሪት ዘፍጥረት 8:1-22 መቅካእኤ

እግዚአብሔር ኖኅንና ከእርሱ ጋር በመርከቡ ውስጥ የነበሩትን አራዊትና እንስሶች ሁሉ አሰበ። ነፋስ በምድር ላይ እንዲነፍስ አደረገ፥ ውኃውም ጎደለ፥ ከምድር በታች ያሉት ታላቅ የውሃ መፍለቂያዎች፥ በሰማይ ያሉት የውሃ መውረጃ በሮች ሁሉ ተዘጉ፤ ዝናቡም ከሰማይ መውረዱን አቆመ። ውሃው ቀስ በቀስ ከምድር ላይ ቀለለ፥ ከመቶ አምሳ ቀንም በኋላ ውኃው ጎደለ። መርከቢቱም በሰባተኛው ወር፥ ከወሩም በዓሥራ ሰባተኛው ቀን በአራራት ተራሮች በአንደኛው ጫፍ ላይ ዐረፈች። ውኃውም እስከ አሥረኛው ወር ድረስ ይጎድል ነበረ፤ በአሥረኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያው ቀን የተራሮቹ ጫፎች ተገለጡ። ከአርባ ቀንም በኋላ ኖኅ የሠራውን የመርከቢቱን መስኮት ከፈተ፥ ቁራንም ወደ ውጪ ላከው፤ እርሱም ውኃው ከምድር ላይ እስኪደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይበር ነበር። ከዚህ በኋላ ኖኅ ውሃው ከምድር ላይ መጉደሉን ለማወቅ አንዲት ርግብ ላከ። ነገር ግን ውሃው ገና ምድርን ሁሉ ሸፍኖ ስለ ነበር ርግቢቱ የምታርፍበት ቦታ አላገኘችም፤ ስለዚህ ኖኅ ወዳለበት መርከብ ተመልሳ መጣች፤ ኖኅም እጁን ዘርግቶ ወደ ውስጥ አስገባት። ሰባት ቀን ከቈየም በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት። ርግብም ወደ ማታ ጊዜ ወደ እርሱ ተመለሰች፥ እነሆም፥ በአፍዋ የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ነበር። ኖኅም ከምድር ላይ ውኃው መጉደሉን አወቀ። ደግሞም ሰባት ቀን ከቈየ በኋላ ርግቢቱን እንደገና አውጥቶ ላካት፤ ዳግመኛም ወደ እርሱ ሳትመለስለት ቀረች። የኖኅ ዕድሜ ስድስት መቶ አንድ በሆነ ጊዜ፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በመጀመሪያው ቀን፥ ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ፤ ኖኅ የመርከቡን ክዳን አንሥቶ ዙሪያውን ተመለከተ፤ ምድሪቱ እንደ ደረቀች አየ። በሁለተኛውም ወር ከወሩም በሀያ ሰባተኛው ቀን ምድር ፈጽማ ደረቀች። እግዚአብሔርም ለኖኅ እንዲህ አለው፦ “አንተ ከሚስትህ፥ ከልጆችህና ከልጆችህ ሚስቶች ጋር ሆነህ ከመርከቡ ውጣ፤ ተራብተውና ተባዝተው ምድርን ሁሉ እንዲሞሉ ከአንተ ጋር ያሉትን ሕያዋን ፍጥረቶች ሁሉ ወፎችን፥ እንስሶችንና ሌሎችን በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ፍጥረቶች ሁሉ ይዘህ ውጣ።” ከዚህ በኋላ ኖኅ ከሚስቱ፥ ከልጆቹና ከልጆቹ ሚስቶች ጋር ሆኖ ከመርከቡ ወጣ፤ አራዊትና እንስሶች፥ ወፎችም በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶችም በየወገናቸው ሆነው ከመርከቡ ወጡ። ኖኅም ለጌታ መሠውያን ሠራ፤ ንጹሕ ከሆኑት እንስሶችና ወፎች ሁሉ ከየዓይነቱ አንዳንድ ወሰደ፤ መሥዋዕት እንዲሆኑም ሁሉንም በመሠዊያው ላይ አቃጠላቸው። የመሥዋዕቱም መዓዛ ጌታን ደስ አሰኘው፤ ጌታም በሐሳቡ እንዲህ አለ፥ “ገና ከታናሽነቱ ጊዜ ጀምሮ የሰው ሐሳብ ክፉ ነውና፥ ሰው በሚፈጽመው በደል ምክንያት ከእንግዲህ ወዲህ ምድርን አልረግምም፤ አሁን እንዳደረግሁት ሕይወት ያለውን ፍጥረት ሁሉ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አላጠፋም። በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ፥ ብርድና ሙቀት፥ በጋና ክረምት፥ ቀንና ሌሊት አያቋርጡም።”